1 ሳሙኤል 4:2-8 NASV

2 ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሰራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፣ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺህ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ።

3 ሰራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፣ ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፣ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ።

4 ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፣በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሰራዊት ጌታ የእግዚእብሔርን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።

5 የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፣ ምድሪቱ እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የደስታ ጩኸት አሰሙ።

6 ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ ጩኸት ሲሰሙ፣ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድ ነው?” ሲሉ ጠየቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤

7 ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቶአል፤ ወዮልን! እንዲህ ዐይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም።

8 ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤