1 ሳሙኤል 6:3-9 NASV

3 እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ከበደል መሥዋዕት ጋር ስደዱት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፤ በዚያ ጊዜ ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ ላይ ለምን እንዳልተነሣ ታውቃላችሁ” አሏቸው።

4 ፍልስጥኤማውያንም፣ “የምንልከው የበደል መሥዋዕት ምን መሆን አለበት?” ሲሉ ጠየቁ።እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተንም ሆነ አለቆቻችሁን የመታው መቅሠፍት አንድ ዐይነት በመሆኑ፣ በፍልስጥኤማውያን ገዦች ቊጥር ልክ አምስት የወርቅ ዕባጮችና አምስት የወርቅ ዐይጦች ላኩ።

5 አገሩን በማጥፋት ላይ ባሉት ዕባጮችና ዐይጦች ዐይነት ምስሎችን ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ እጁን ከእናንተ፣ ከአማልክታችሁና ከምድራችሁ ላይ ያነሣ ይሆናል።

6 እንደ ግብፃውያንና እንደ ፈርዖን ልባችሁን የምታደነድኑት ለምንድን ነው? እነርሱም እስራኤላውያንን የለቀቋቸው እግዚአብሔር በጽኑ ከቀጣቸው በኋላ አይደለምን?

7 “ስለዚህ አዲስ ሠረገላና ቀንበር ያልተ ጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞች አዘጋጁ። ላሞቹን በሠረገላው ጥመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ወደ ቤት መልሷቸው።

8 የእግዚአብሔርን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ በታቦቱም አጠገብ ባለው ሣጥን ውስጥ ለበደል መሥዋዕት የምትልኩትን የወርቅ ምስሎች አስቀምጡ፤ በፈለገውም መንገድ እንዲሄድ ልቀቁት፤

9 ነገር ግን ወዴት እንደሚሄድ ተመልከቱ፤ ወደ ቤትሳሚስ አቅጣጫ ወደ ገዛ አገሩ የሚሄድ ከሆነ፣ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው። ወደዚያ ካልሄደ ግን፣ መከራው በአጋጣሚ የደረሰብን እንጂ የእርሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን።”