1 ሳሙኤል 7:1-6 NASV

1 የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወጡ፤ ከዚያም በኰረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት ወሰዱት። የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።

2 ታቦቱ በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ ረዥም ጊዜ ሆነው፤ በአጠቃላይ ሃያ ዓመት ቈየ። የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አዘነ፤ እግዚአብሔርንም ፈለገ።

3 ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፣ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው።

4 ስለዚህ እስራኤላውያን የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አስወግደው፣ እግዚአብሔርን ብቻ አመለኩ።

5 ከዚያ በኋላ ሳሙኤል፣ “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ” አለ።

6 እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ውሃ ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፤ በዚያች ዕለት ጾሙ፤ በዚያም “እግዚአብሔርን በድለናል” ብለው ተናዘዙ። ሳሙኤልም በምጽጳ እስራኤልን ይፈርድ ነበር።