1 ሳሙኤል 7:2-8 NASV

2 ታቦቱ በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ ረዥም ጊዜ ሆነው፤ በአጠቃላይ ሃያ ዓመት ቈየ። የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አዘነ፤ እግዚአብሔርንም ፈለገ።

3 ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፣ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው።

4 ስለዚህ እስራኤላውያን የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አስወግደው፣ እግዚአብሔርን ብቻ አመለኩ።

5 ከዚያ በኋላ ሳሙኤል፣ “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ” አለ።

6 እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ውሃ ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፤ በዚያች ዕለት ጾሙ፤ በዚያም “እግዚአብሔርን በድለናል” ብለው ተናዘዙ። ሳሙኤልም በምጽጳ እስራኤልን ይፈርድ ነበር።

7 እስራኤል በምጽጳ መሰብሰባቸውን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ የፍልስጥኤማውያን ገዦች ሊወጓቸው ወጡ፤ እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ፣ ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ፤

8 ሳሙኤልንም፣ “አምላካችን እግዚአብሔር ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ወደ እርሱ መጸለይህን አታቋርጥ” አሉት።