ሚልክያስ 2:2-8 NASV

2 ባትሰሙ፣ ልባችሁንም ስሜን ለማክበር ባታዘጋጁ፣ ርግማን እሰድባችኋለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ መርገም እለውጠዋለሁ፤ ልታከብሩኝ ልባችሁን አላዘጋጃችሁምና’ ረግሜዋለሁ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

3 “ዘራችሁን እገሥጻለሁ፤ የመሥዋታችሁን ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተም ከእርሱ ጋር ትወገዳላችሁ፤

4 ከሌዊ ጋር የገባሁት ኪዳን ይጸና ዘንድ፣ ይህን ማስጠንቀቂያ የላክሁት እኔ መሆኔንም ታውቃላችሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

5 “ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳን የሕይወትና የሰላም ኪዳን ነበር፤ እነርሱንም ሰጠሁት፤ ይህም ክብርን አመጣ፤ እርሱም አከበረኝ፤ ስሜንም በመፍራትም ጸና።

6 እውነተኛ ትምህርት በአፉ ነበር፤ ምንም ዐይነት የሐሰት ነገር በአንደበቱ አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ተራመደ፤ ብዙዎችንም ከኀጢአት መለሰ።

7 “ካህኑ የሁሉ ገዥ፣ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ስለ ሆነ ከንፈሮቹ ዕውቀትን ሊጠብቁ፣ ሰዎችም ከአንደበቱ ትምህርትን ሊፈልጉ ይገባል፤

8 እናንተ ግን ከመንገዱ ወጥታችኋል፤ በትምህርታችሁም ብዙዎች እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል፤ የሌዊንም ኪዳን አፍርሳችኋል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።