ሚክያስ 6:2-8 NASV

2 ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ክስ አድምጡ፤እናንት የምድር ጽኑ መሠረቶችም፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፤ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳል።

3 “ሕዝቤ ሆይ፤ ምን አድርጌሃለሁ?ሸክም የሆንሁብህስ እንዴት ነው?እስቲ መልስልኝ!

4 ከግብፅ አወጣሁህ፤ከባርነት ምድርም ተቤዠሁህ፤እንዲመሩህ ሙሴን፣አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ።

5 ሕዝቤ ሆይ፤የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፣የቢዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትንም እስቲ አስቡ፤ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሥራ ታውቁ ዘንድ፣ከሰጢም እስከ ጌልገላ የተጓዛችሁትን አስቡ።

6 ምን ይዤበእግዚአብሔር ፊት ልቅረብ፣በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ?የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ከአንድ ዓመት ጥጃ ጋር ይዤ በፊቱ ልቅረብን?

7 በአንድ ሺህ አውራ በጎች፣በዐሥር ሺህ የዘይት ፈሳሽ እግዚአብሔር ደስ ይለዋልን?ስለ በደሌ የበኵር ልጄን፣ስለ ነፍሴም ኀጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብለትን?

8 ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?