ሚክያስ 6 NASV

የእግዚአብሔር ክስ በእስራኤልን ላይ

1 እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ፤“ተነሡ፤ ጒዳያችሁን በተራሮችም፤ፊት አቅርቡ፤ኰረብቶች እናንተ የምትሉትን ይስሙ፤

2 ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ክስ አድምጡ፤እናንት የምድር ጽኑ መሠረቶችም፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፤ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳል።

3 “ሕዝቤ ሆይ፤ ምን አድርጌሃለሁ?ሸክም የሆንሁብህስ እንዴት ነው?እስቲ መልስልኝ!

4 ከግብፅ አወጣሁህ፤ከባርነት ምድርም ተቤዠሁህ፤እንዲመሩህ ሙሴን፣አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ።

5 ሕዝቤ ሆይ፤የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፣የቢዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትንም እስቲ አስቡ፤ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሥራ ታውቁ ዘንድ፣ከሰጢም እስከ ጌልገላ የተጓዛችሁትን አስቡ።

6 ምን ይዤበእግዚአብሔር ፊት ልቅረብ፣በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ?የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ከአንድ ዓመት ጥጃ ጋር ይዤ በፊቱ ልቅረብን?

7 በአንድ ሺህ አውራ በጎች፣በዐሥር ሺህ የዘይት ፈሳሽ እግዚአብሔር ደስ ይለዋልን?ስለ በደሌ የበኵር ልጄን፣ስለ ነፍሴም ኀጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብለትን?

8 ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?

የእስራኤል በደልና ቅጣት

9 ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ስሙ! እግዚአብሔር ከተማዪቱን እንዲህ እያለ ይጣራል፤“በትሩን አስቡ፤ ያዘጋጀውም ማን እንደሆነ አስታውሱ።

10 የክፋት ቤት ሆይ፤በግፍ የተገኘ ሀብታችሁን፣በሐሰተኛ መስፈሪያ የሰበሰባችሁትን አስጸያፊ ነገር እረሳዋለሁን?

11 አባይ ሚዛን የያዘውን ሰው፣ሐሰተኛ መመዘኛ በከረጢት የቋጠረውን ንጹሕ ላድርገውን?

12 ባለጠጎቿ ግፈኞች፣ሰዎችዋ ሐሰተኞች ናቸው፤ምላሳቸውም አታላይ ናት።

13 ስለዚህ አንተን አጠፋሃለሁ፣ከኀጢአትህ የተነሣ አፈራርስሃለሁ።

14 ትበላለህ፤ ነገር ግን አትጠግብም፤ሆድህ እንዳለ ባዶውን ይቀራል፤ታከማቻለህ፤ ነገር ግን አይጠራቀምልህም፤የሰበሰብኸውን ለሰይፍ አደርገዋለሁና።

15 ትዘራለህ፤ ነገር ግን አታጭድም፤የወይራ ዘይት ትጨምቃለህ፤ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ወይንን ትቈርጣለህ፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ አትጠጣም።

16 የዖምሪን ሥርዐት፣የአክዓብን ቤት ልምድ ሁሉ የሙጥኝ ብለሃል፤ትውፊታቸውንም ተከትለሃል።ስለዚህ አንተን ለውድመት፣ሕዝብህን ለመዘባበቻ አሳልፌ እሰጣለሁ፤አሕዛብም ይሣለቁብሃል።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7