ሚክያስ 7:1-7 NASV

1 ለእኔ ወዮልኝ!የወይን ዕርሻ በሚቃረምበት ጊዜየበጋ ፍራፍሬ እንደሚለቅም ሰው ሆኛለሁ፤የሚበላ የወይን ዘለላ የለም፤የምንጓጓለት፣ ቶሎ የሚደርሰው በለስም አልተገኘም።

2 ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ከምድር ጠፍቶአል፤አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፣ሰው ሁሉ ደም ለማፍሰስ ያደባል፤እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል።

3 እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ገዡ እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ፈራጁ ጒቦ ይቀበላል፤ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ።

4 ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት ነው፤የጠባቂዎቻችሁ ቀን ደርሶአል፤የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መጥቶአል፤የሚሸበሩበትም ጊዜ አሁን ደርሶአል።

5 ባልንጀራህን አትመን፤በጓደኛህም አትታመን፤በዕቅፍህ ለምትተኛዋ እንኳ፣ስለምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ።

6 ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፤ምራት በአማቷ ላይ ትነሣለች፤የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ ናቸውና።

7 እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ፤አምላኬ ይሰማኛል።