ሚክያስ 7:2-8 NASV

2 ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ከምድር ጠፍቶአል፤አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፣ሰው ሁሉ ደም ለማፍሰስ ያደባል፤እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል።

3 እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ገዡ እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ፈራጁ ጒቦ ይቀበላል፤ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ።

4 ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት ነው፤የጠባቂዎቻችሁ ቀን ደርሶአል፤የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መጥቶአል፤የሚሸበሩበትም ጊዜ አሁን ደርሶአል።

5 ባልንጀራህን አትመን፤በጓደኛህም አትታመን፤በዕቅፍህ ለምትተኛዋ እንኳ፣ስለምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ።

6 ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፤ምራት በአማቷ ላይ ትነሣለች፤የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ ናቸውና።

7 እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ፤አምላኬ ይሰማኛል።

8 ጠላቴ ሆይ፤ በእኔ ላይ በደረሰው ደስ አይበልሽ!ብወድቅም እንኳ እነሣለሁ፤በጨለማ ብቀመጥ እንኳ፣ እግዚአብሔር ብርሃኔ ይሆናል።