1 ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነሽ!እንዴትስ ያለሽ ቈንጆ ነሽከመሸፈኛሽ ውስጥ ያሉት ዐይኖችሽእንደ ርግብ ዐይኖች ናቸው፤ጠጒርሽም ከገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ፣የፍየል መንጋ ነው።
2 ጥርሶችሽ ወዲያው ተሸልተው፣ከመታጠቢያ እንደ ወጡ የበግ መንጋ ናቸው፤ሁሉም መንታ መንታ የወለዱ፣ከመካከላቸውም መካን የሌለባቸው ናቸው።
3 ከንፈሮችሽ ቀይ የሐር ፈትል ይመስላሉ፤አፍሽም ውብ ነው፤ከመሸፈኛሽ ውስጥ ያሉት ጒንጮችሽ፣ለሁለት የተከፈለ ሮማን ይመስላሉ።
4 ዐንገትሽ አምሮ የተሠራውን፣በላዩም የጦረኞች ጋሻዎች ሁሉ ያሉበትን፣ሺህ ጋሻዎች የተንጠለጠሉበትን፣የዳዊትን የመጠበቂያ ማማ ይመስላል።
5 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ ሆነው የተወለዱ፣በውብ አበቦች መካከልም የተሰማሩ፣ሁለት የሚዳቋ ግልገሎችን ይመስላሉ።
6 ጎሕ ከመቅደዱ በፊት፣ጥላውም ሳይሸሽ፣ወደ ከርቤ ተራራ፣ወደ ዕጣኑም ኰረብታ እወጣለሁ።