15 ኑኃሚን መልሳ፣ “እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች፤ አብረሻት ተመለሽ” አለቻት።
16 ሩት ግን እንዲህ አለች፤ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል።
17 በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ እዚያው እቀበራለሁ። ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።”
18 ሩት አብራት ለመሄድ መቊረጧን በተረዳች ጊዜ፣ ኑኃሚን መጐትጐቷን ተወች።
19 ከዚያም ሁለቱ ሴቶች እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ተጓዙ፤ ቤተ ልሔም እንደ ደረሱም፣ በእነርሱ ምክንያት ከተማው በሙሉ ተተረማመሰ፤ ሴቶቹም፣ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” በማለት ተገረሙ።
20 እርሷም እንዲህ አለች፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን እጅግ መራራ አድርጎታልና ማራ በሉኝ እንጂ፣ ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ።
21 በሙላት ወጣሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አስጨንቆኝ፣ ሁሉን የሚችል አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ እንዴት ኑኃሚን ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?” አለቻቸው።