ሩት 3:12-18 NASV

12 ምንም እንኳ እኔ ቅርብ የሥጋ ዘመድ መሆኔ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ከእኔ ይልቅ መቤዠት የሚገባው ቅርብ የሥጋ ዘመድ አለ።

13 ከዚህ ዕደሪ፤ ሲነጋም ሰውየው ሊቤዥሽ ከፈለገ፣ መልካም ነው ይቤዥሽ፤ የማይፈልግ ከሆነ ግን በሕያው እግዚአብሔር እምላለሁ፤ እኔ እቤዥሻለሁ፤ እስኪነጋም ድረስ እዚሁ ተኚ።”

14 ስለዚህም ሩት እስኪነጋ ድረስ እግርጌው ተኛች፤ ዳሩ ግን ማንም ሰው ተለይቶ ሊታወቅ በማይችልበት ሰዓት ቀደም ብላ ተነሣች፤ እርሱም፣ “ሴት ወደዚህ ዐውድማ መምጣቷ እንዳይታወቅ” አላት።

15 እንዲሁም፣ “በላይሽ የደረብሽውን ልብስ አቅርቢልኝ፤ ዘርግተሽም ያዢው” አላት፤ ዘርግታ እንደ ያዘችም፤ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፍሮ አሸከማት፤ ከዚያም ወደ ከተማ ተመለሰች።

16 ሩት ወደ አማቷ እንደ ተመለሰች፣ ኑኃሚን፣ “ልጄ ሆይ፤ የሄድሽበት ጒዳይ እንዴት ሆነ?” ብላ ጠየቀቻት።ሩትም ቦዔዝ ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት፤

17 ቀጥላም፣ “ ‘ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትመለሺ’ በማለት ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ” አለቻት።

18 ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ የሚሆነውን ነገር እስክታውቂ ድረስ ታገሺ፤ ጒዳዩ ዛሬውኑ እልባት ካላገኘ ሰውየው አያርፍም” አለቻት።