ሩት 4:11-17 NASV

11 ከዚያም ሽማግሌዎቹና በከተማዪቱ በር አደባባይ የነበሩት ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት፣ የእስራኤልን ቤት በአንድነት እንደሠሩ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ የበረታህ ሁን፤ ስምህም በቤተልሔም የተጠራ ይሁን።

12 እግዚአብሔር ከዚህች ወጣት ሴት በሚሰጥህ ዘር አማካይነት፣ ቤተ ሰብህን ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤተ ሰብ ያድርገው።”

13 ስለዚህ ቦዔዝ ሩትን ወሰዳት፤ ሚስቱም ሆነች። ከዚያም ወደ እርሷ ገባ፤ እግዚአብሔር እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች።

14 ሴቶቹም ኑኃሚንን እንዲህ አሏት፤ “ዛሬ የሚቤዥ ቅርብ የሥጋ ዘመድ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ በመላው እስራኤልም ስሙ ይግነን።

15 ልጁ ሕይወትሽን ያድሳታል፤ በእርጅና ዘመንሽም ይጦርሻል፤ የምትወድሽና ከሰባት ወንዶች ልጆች የምትበልጥብሽ ምራትሽ ወልዳዋለችና።”

16 ከዚያም ኑኃሚን ሕፃኑን ተቀብላ ታቀፈችው፤ ሞግዚትም ሆነችው።

17 ጎረቤቶቿ የሆኑ ሴቶችም፣ “ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት” አሉ። ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት፤ እርሱም የዳዊት አባት የሆነው የእሴይ አባት ነበር።