ሩት 4:5-11 NASV

5 ከዚያም ቦዔዝ፣ “እንግዲህ መሬቱን ከኑኃሚንና ከሞዓባዊቷ ከሩት ላይ በምትገዛበት ዕለት የሟቹን ስም በርስቱ ለማስጠራት ሚስቱንም አብረህ መውሰድ አለብህ” አለው።

6 ያም ቅርብ የሥጋ ዘመድ፣ “እንዲህ ከሆነማ የራሴን ርስት አደጋ ላይ ልጥል ስለምችል፣ እኔ ልቤዠው አልችልም፤ አንተው ራስህ ተቤዠው” አለው።

7 በጥንት ዘመን በእስራኤል የመቤዠትም ሆነ ንብረት የማስተላለፍ ጒዳይ የሚጸናው አንዱ ወገን ጫማውን አውልቆ ለሌላው ወገን ሲሰጠው ነው፤ በእስራኤል ዘንድ መሸጥም ሆነ መግዛት ሕጋዊነት የሚኖረው በዚህ ሁኔታ ነበር።

8 ቅድሚያ ያለው ቅርብ የሥጋ ዘመድም ቦዔዝን፣ “እንግዲህ አንተው ራስህ ግዛው” ብሎ ጫማውን አወለቀ።

9 ቦዔዝም ለሽማግሌዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የአቤሜሌክን፣ የኬሌዎንንና የመሐሎንን ንብረት በሙሉ ከኑኃሚን ላይ ለመግዛቴ፣ በዛሬው ዕለት እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤

10 እንዲሁም የሟቹ ስም ከወንድሞቹ መካከልና ከአገሩ ደጅ እንዳይጠፋ፣ የሟቹን ስም በርስቱ ላይ ለማስጠራት የመሐሎን ሚስት የነበረችው ሞዓባዊት ሩትን አግብቼአታለሁ፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።”

11 ከዚያም ሽማግሌዎቹና በከተማዪቱ በር አደባባይ የነበሩት ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት፣ የእስራኤልን ቤት በአንድነት እንደሠሩ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ የበረታህ ሁን፤ ስምህም በቤተልሔም የተጠራ ይሁን።