ሩት 4:9-15 NASV

9 ቦዔዝም ለሽማግሌዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የአቤሜሌክን፣ የኬሌዎንንና የመሐሎንን ንብረት በሙሉ ከኑኃሚን ላይ ለመግዛቴ፣ በዛሬው ዕለት እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤

10 እንዲሁም የሟቹ ስም ከወንድሞቹ መካከልና ከአገሩ ደጅ እንዳይጠፋ፣ የሟቹን ስም በርስቱ ላይ ለማስጠራት የመሐሎን ሚስት የነበረችው ሞዓባዊት ሩትን አግብቼአታለሁ፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።”

11 ከዚያም ሽማግሌዎቹና በከተማዪቱ በር አደባባይ የነበሩት ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት፣ የእስራኤልን ቤት በአንድነት እንደሠሩ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ የበረታህ ሁን፤ ስምህም በቤተልሔም የተጠራ ይሁን።

12 እግዚአብሔር ከዚህች ወጣት ሴት በሚሰጥህ ዘር አማካይነት፣ ቤተ ሰብህን ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤተ ሰብ ያድርገው።”

13 ስለዚህ ቦዔዝ ሩትን ወሰዳት፤ ሚስቱም ሆነች። ከዚያም ወደ እርሷ ገባ፤ እግዚአብሔር እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች።

14 ሴቶቹም ኑኃሚንን እንዲህ አሏት፤ “ዛሬ የሚቤዥ ቅርብ የሥጋ ዘመድ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ በመላው እስራኤልም ስሙ ይግነን።

15 ልጁ ሕይወትሽን ያድሳታል፤ በእርጅና ዘመንሽም ይጦርሻል፤ የምትወድሽና ከሰባት ወንዶች ልጆች የምትበልጥብሽ ምራትሽ ወልዳዋለችና።”