ሰቆቃወ 2:3-9 NASV

3 በጽኑ ቍጣው፣የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ሰበረ፤ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ።

4 እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤ቀኝ እጁ ተዘጋጅታለች፤ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤እንደ ጠላት ዐረዳቸው፤በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ላይ፣ቍጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።

5 እግዚአብሔር እንደ ጠላት ሆነ፤እስራኤልንም ዋጠ፤ቤተ መንግሥቶቿን ሁሉ ዋጠ፤ምሽጎቿን አፈራረሰ፤በይሁዳ ሴት ልጅ፣ለቅሶንና ሰቈቃን አበዛ።

6 ማደሪያውን እንደ አትክልት ስፍራ ባዶ አደረገ፤መሰብሰቢያ ስፍራውን አፈረሰ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን፣ዓመት በዓላቶቿንና ሰንበታቷን እንድትረሳ አደረጋት፤በጽኑ ቍጣው፣ንጉሡንና ካህኑን እጅግ ናቀ።

7 እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤መቅደሱንም ተወ፤የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤በዓመት በዓል ቀን እንደሚደረገው በእግዚአብሔር ቤት በኀይል ጮኹ።

8 በጽዮን ሴት ልጅ ዙሪያ ያለውን ቅጥር፣ እግዚአብሔር ለማፍረስ ወሰነ፤የመለኪያ ገመድ ዘረጋ፤ከማጥፋትም እጆቹን አልሰበሰበም፤ምሽጎችና ቅጥሮች እንዲያለቅሱ አደረገ፤በአንድነትም ጠፉ።

9 በሮቿ ወደ ምድር ሰመጡ፤የብረት መወርወሪያዎቻቸውን ሰባበረ፤ አጠፋቸውም፤ንጉሥዋና መሳፍንቶቿ በአሕዛብ መካከል ተማርከው ተሰደዋል፤ሕጉ ከእንግዲህ አይኖርም፤ነቢያቶቿም ከእንግዲህ፣ ከእግዚአብሔር ራእይ አያገኙም።