ነህምያ 13:20-26 NASV

20 የልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎችና ቸርቻሪዎች ከኢየሩሳሌም ውጭ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ አድረዋል።

21 እኔ ግን፣ “ከቅጥሩ ውጭ የምታድሩት ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ዳግመኛ ብታደርጉ እጄን አነሣባችኋለሁ” ስል አስጠነቀቅኋቸው፤ እነርሱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰንበት ቀን አልመጡም።

22 ከዚያም ሌዋውያኑ ራሳቸውን እንዲያነጹ፣ ሄደውም የቅጥሩን በር እንዲጠብቁና የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ አዘዝኋቸው።አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህም ደግሞ አስበኝ፤ እንደ ታላቅ ፍቅርህም ብዛት ምሕረት አድርግልኝ።

23 በእነዚያም ቀናት የአሽዶድን፣ የአሞንንና የሞዓብን ሴቶች ያገቡ አይሁድ አገኘሁ።

24 ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ የአሽዶድን፣ ወይም ከሌሎቹ ሕዝቦች የአንዱን ቋንቋ እንጂ የአይሁድን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር።

25 እኔም ገሠጽኋቸው፤ ርግማንም አወረድሁባቸው። አንዳንዶቹን መታኋቸው፤ ጠጒራቸውንም ነጨሁ። በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ስል አማልኋቸው፤ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ።

26 የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ኀጢአት የሠራው እንዲህ ከመሰለው ጋብቻ የተነሣ አይደለምን? በብዙ መንግሥታት መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤ በአምላኩም የተወደደ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ አደረገው። ነገር ግን ባዕዳን ሴቶች ወደ ኀጢአት መሩት።