ነህምያ 3:1-6 NASV

1 ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ማማ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ማማ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤

2 ቀጥሎ ያለውንም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ እነርሱ ከሠሩት ቀጥሎ ደግሞ የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።

3 የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።

4 የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤

5 የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሐ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንቶቻቸው ግን በተቈጣ ጣሪ አሠሪዎቻቸው ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም።

6 አሮጌውን በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።