ነህምያ 3:16-22 NASV

16 ከእርሱም በኋላ የቤት ጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር ትይዩ እስከ ሰው ሠራሹ ኵሬና “የጀግኖች ቤት” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን መልሶ ሠራ።

17 ከእርሱ ቀጥሎ ሌዋውያኑ በባኒ ልጅ በሬሁ ሥር ሆነው የዕድሳት ሥራ ሠሩ። ከእርሱ ቀጥሎ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ ሐሸብያ አውራጃውን መልሶ ሠራ።

18 ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ደግሞ የሌላው የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይና በእርሱም ሥር የነበሩት የአገሩ ሰዎች መልሰው ሠሩ።

19 ከእርሱም ቀጥሎ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በሚያወጣውና እስከ ማእዘኑ በሚደርሰው ትይዩ ያለውን ሌላ ክፍል የምጽጳ ገዥ የኢያሱ ልጅ ኤጽር መልሶ ሠራ።

20 ከእርሱም ቀጥሎ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማእዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህኑ እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ያለውን ሌላ ክፍል በትጋት መልሶ ሠራ።

21 ከእርሱ ቀጥሎ ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ያለውን ሌላ ክፍል የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት መልሶ ሠራ።

22 ከእርሱም ቀጥሎ ያለውን ክፍል ከአካባቢው የመጡት ካህናት መልሰው ሠሩ።