ነህምያ 3:26-32 NASV

26 በዖፌል ኰረብታ ላይ የሚኖሩት የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች “የውሃ በር” ተብሎ ከሚጠራው ትይዩ ጀምሮ በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው ግንብ ድረስ መልሰው ሠሩ።

27 ከእነርሱ ቀጥሎ የቴቁሐ ሰዎች ከታላቁ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላ ክፍል መልሰው ሠሩ።

28 “የፈረስ በር” ተብሎ ከሚጠራው በላይ ያለውን ደግሞ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ትይዩ ያለውን መልሰው ሠሩ።

29 ከእነርሱም ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሴኬንያ ልጅ ሸማያ መልሶ ሠራ።

30 ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል ደግሞ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኖን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ከመኖሪያው ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ።

31 ከእርሱ ቀጥሎ ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ መልክያ በመቈጣጠሪያው በር ትይዩ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት፣ እንዲሁም ከማእዘኑ በላይ እስከሚገኘው ክፍል ያለውን መልሶ ሠራ፤

32 ከማእዘኑ በላይ ከሚገኘው ክፍል ጀምሮ እስከ በጎች በር ያለውን ደግሞ ወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹ መልሰው ሠሩ።