9 ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።
10 አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ።
11 እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ።
12 በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦብያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ።
13 በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው።
14 አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦብያንና ሰንባላጥን አስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም አስብ።
15 ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ አምስተኛ ቀን፣ በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ።