ነህምያ 9:13-19 NASV

13 “በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው።

14 የተቀደሰች ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዞችን፣ ሥርዐቶችንና ሕጎችን በባሪያህ በሙሴ አማካይነት ሰጠሃቸው።

15 በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው።

16 “እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕ ተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም።

17 ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤

18 የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብፅ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።

19 “ከርኅራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ ቀን የደመናው ዐምድ በመንገዳቸው ላይ መምራቱን፣ ሌሊትም የእሳቱ ዐምድ በሚሄዱበት ላይ ማብራቱን አላቆመም።