ነህምያ 9:3-9 NASV

3 በያሉበትም ቦታ ቆመው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሩብ ቀን አነበቡ፤ የቀረውን ሩብ ቀን ደግሞ ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመስገድ አሳለፉ።

4 ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ቀድምኤል፣ ሰበንያ፣ ቡኒ፣ ሰራብያ፣ ባኒ፣ ከናኒ፣ በመውጫ ደረጃዎች ላይ ቆሙ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅ ጮኹ።

5 ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ።“ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል።

6 አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል።

7 “አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳው ያንዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ።

8 ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርጌሳውያንን ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ።

9 “አንተ በግብፅ የአባቶቻችንን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ።