4 ሠረገሎች በአደባባይ ወዲያ ወዲህ ይከንፋሉ፤በመንገዶችም ላይ ይርመሰመሳሉ፤የሚንበለበል ፋና ይመስላሉ፤እንደ መብረቅም ይወረወራሉ።
5 ምርጥ ተዋጊዎቹን ይጠራል፤ዳሩ ግን መንገድ ላይ ይሰናከላሉ፤ወደ ከተማዪቱ ቅጥር ይሮጣሉ፤መከላከያ ጋሻውም በቦታው አለ።
6 የወንዙ በር ወለል ብሎ ተከፈተ፤ቤተ መንግሥቱም ወደቀ።
7 ከተማዪቱ መማረኳና መወሰዷ እንደማይቀር፣አስቀድሞ ተነግሮአል፤ሴቶች ባሪያዎቿ እንደ ርግብ ያለቅሳሉ፤ደረታቸውንም ይደቃሉ።
8 ነነዌ እንደ ኵሬ ናት፤ውሃዋም ይደርቃል፤“ቁም! ቁም!” ብለው ይጮኻሉ፤ነገር ግን ወደ ኋላ የሚመለስ የለም።
9 ብሩን ዝረፉ፤ወርቁን ንጠቍ፤በየግምጃ ቤቱ ያለው፤የተከማቸውም ሀብት ስፍር ቍጥር የለውም።
10 ተበዝብዛለች፤ ተዘርፋለች፤ ተራቍታለች።ልብ ቀልጦአል፤ ጒልበት ተብረክርኮአል፤ሰውነት ተንቀጥቅጦአል፤ ፊት ሁሉ ገርጥቶአል።