1 ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤
2 እናንት ሽማግሌዎች፣ ይህን ስሙ፤በምድሪቱም የምትኖሩ ሁላችሁ፣ አድምጡ፤በእናንተ ዘመን፣ ሆነ በአባቶቻችሁም ዘመን፣እንዲህ ዐይነት ነገር ሆኖ ያውቃልን?
3 ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤ልጆቻችሁ ለልጆቻቸው ይንገሩ፤ልጆቻቸውም ለሚቀጥለው ትውልድ ይንገሩ።
4 ከአንበጣ መንጋ የተረፈውን፣ትልልቁ አንበጣ በላው፤ከትልልቁ አንበጣ የተረፈውን፣ኵብኵባ በላው፤ከኵብኵባ የተረፈውን፣ሌሎች አንበጦች በሉት።
5 እናንት ሰካራሞች፤ ተነሡ፤ አልቅሱ፤እናንት የወይን ጠጅ ጠጪዎች ሁሉ፤ ዋይ በሉ፤ስለ አዲሱ የወይን ጠጅ ዋይ ብላችሁ አልቅሱ፤አፋችሁ ላይ እንዳለ ተነጥቃችኋልና።