ዳንኤል 11:24-30 NASV

24 የበለጸጉትን ክፍለ አገሮች በሰላም ሳሉ በድንገት ይወርራቸዋል፤ አባቶቹም ሆኑ አያቶቹ ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል፤ ይከናወንለታልም፤ ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና የተገኘውን ሀብት ሁሉ ለተከታዮቹ ያካፍላቸዋል፤ ምሽጎችን ለመጣል ያሤራል፤ ይህን የሚያደርገውም ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።

25 “ታላቅ ሰራዊት አደራጅቶ ኀይሉንና ብርታቱን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያነሣሣል፤ የደቡብ ንጉሥም ቊጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኀያል ሰራዊት ይዞ ጦርነትን ያውጃል፤ ነገር ግን ከተዶለተበት ሤራ የተነሣ መቋቋም አይችልም።

26 ከንጉሥ ማዕድ አብረውት ሲበሉ የነበሩት ሊያጠፉት ያሤራሉ፤ ሰራዊቱም ይደመሰሳል፤ ብዙዎቹም በጦርነት ይወድቃሉ።

27 ልባቸው ወደ ክፋት ያዘነበለው ሁለቱ ነገሥታት፣ በአንድ ገበታ አብረው ይቀመጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ሐሰትን ይነጋገራሉ፤ ነገር ግን የተወሰነው ጊዜ ገና ስለ ሆነ አይከናወንላቸውም።

28 የሰሜን ንጉሥ ብዙ ሀብት ይዞ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል፤ ነገር ግን ልቡ በተቀደሰው ኪዳን ላይ ይነሣሣል፤ ክፉ ነገርም ያደርግበታል፤ ከዚያም ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

29 “በተወሰነው ጊዜ ደቡቡን እንደ ገና ይወራል፤ በዚህ ጊዜ ግን ውጤቱ ከበፊቱ የተለየ ይሆናል።

30 የኪቲም መርከቦች ይቃወሙታል፤ ልቡም ይሸበራል። ወደ ኋላም ይመለሳል፤ ቊጣውን በተቀደሰው ኪዳን ላይ ያወርዳል፤ ተመልሶም የተቀደሰውን ኪዳን የተውትን ይንከባከባል።