ዳንኤል 10 NASV

ዳንኤል በራእይ ያየው ሰው

1 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ ብልጣሶር ለተባለው ዳንኤል ራእይ ታየው። መልእክቱ እውነት ነው፤ ስለ ታላቅ ጦርነትም የሚገልጽ ነበረ። መልእክቱንም ይገነዘብ ዘንድ በራእይ ማስተዋል ተሰጠው።

2 በዚያን ጊዜ እኔ ዳንኤል ለሦስት ሳምንት አለቀስሁ፤

3 ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ምርጥ ምግብ አልበላሁም፤ ሥጋም ሆነ የወይን ጠጅ ወደ አፌ አልገባም፤ ቅባትም አልተቀባሁም።

4 በመጀመሪያው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ በታላቁ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ቆሜ፣

5 ቀና ብዬ ስመለከት፣ በፊቴ በፍታ የለበሰና በወገቡም ላይ ምርጥ የወርቅ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ።

6 አካሉ እንደ ዕንቍ፣ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዐይኖቹ እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደ ጋለ ናስ የሚያብረቀርቁ፣ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር።

7 ራእዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ፍርሀት ስለወደቀባቸው ሸሽተው ተደበቁ።

8 ስለዚህ ይህን ታላቅ ራእይ እያየሁ ብቻዬን ቀረሁ፤ ምንም ጒልበት አልነበረኝም፤ መልኬ እጅጉን ገረጣ፤ ኀይልም አጣሁ።

9 ከዚያም የቃሉን ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ፣ በግምባሬ በምድር ላይ ተደፍቼ በከባድ እንቅልፍ ተዋጥሁ።

10 እነሆም፣ አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤ እየተንቀጠቀጥሁም በእጄና በጒልበቴ አቆመኝ፤

11 እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ፣ አሁን ወዳንተ ተልኬአለሁና፣ የምነግርህን አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም” አለኝ። ይህን ሲለኝም፣ እየተንቀጠቀጥሁ ተነሥቼ ቆምሁ።

12 ደግሞም እንዲህ አለኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አትፍራ፣ ማስተዋልን ለማግኘትና በአምላክህም ፊት ራስህን ለማዋረድ ከወሰንህበት ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም የቃልህን መልስ ይዤ መጥቻለሁ።

13 ነገር ግን የፋርስ መንግሥት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም በዚያ ከፋርስ ንጉሥ ጋር ተውሁት።

14 ራእዩ ሊፈጸም ገና ብዙ ዘመን ስለሚቀረው፣ ወደ ፊት በሕዝብህ ላይ የሚሆነውን ልገልጽልህ አሁን ወደ አንተ መጥቻለሁ።”

15 ይህን እየተናገረኝ ሳለ፣ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፤ የምናገረውንም አጣሁ።

16 ከዚያም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እኔም አፌን ከፈትሁ፤ መናገርም ጀመርሁ፤ በፊቴ የነበረውንም እንዲህ አልሁት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ከራእዩ የተነሣ ተሠቃይቻለሁ፤ ኀይልም አጣሁ፤

17 ጌታዬ ሆይ፤ ጒልበቴ ከዳኝ፤ መተንፈስም አቅቶኛል፣ እኔ አገልጋይህ ከአንተ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ?”

18 እንደ ገናም፣ ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም።

19 እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና” አለኝ።እየተናገረኝም ሳለ፣ በረታሁና፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አበርትተኸኛልና ተናገር” አልሁት።

20 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ለምን ወደ አንተ እንደ መጣሁ ታውቃለህ? የፋርስን አለቃ ለመውጋት በቶሎ እመለሳለሁ፤ እኔም ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል።

21 አስቀድሜ ግን በእውነት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ ከእነዚህ አለቆች ጋር ለመዋጋት ከአለቃችሁ ከሚካኤል በስተቀር የሚረዳኝ የለም።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12