ዳንኤል 11:7-13 NASV

7 “ከዘመዶቿ አንዱ ስፍራዋን ሊይዝ ይነሣል፤ የሰሜንን ንጉሥ ሰራዊት ይወጋል፤ ምሽጎቹንም ጥሶ ይገባል፤ ከእነርሱም ጋር ተዋግቶ ድል ያደርጋል።

8 አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብፅም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ከመዋጋት ይቈጠባል።

9 የሰሜኑም ንጉሥ፣ የደቡቡን ንጉሥ ግዛት ይወራል፤ ነገር ግን አፈግፍጎ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

10 ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እስከ ጠላት ምሽግ ደርሶ የሚዋጋና ሊቋቋሙት እንደማይቻል ጐርፍ የሚጠራርግ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባሉ።

11 “ከዚያም የደቡቡ ንጉሥ በቊጣ ወጥቶ የሰሜኑን ንጉሥ ይወጋል። የሰሜኑ ንጉሥ ታላቅ ሰራዊት ቢያሰባስብም ይሸነፋል።

12 የደቡቡ ንጉሥ ብዙ ሰራዊት በሚማርክበት ጊዜ ልቡ በትዕቢት ይሞላል፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችንም ይገድላል፤ ነገር ግን በድል አድራጊነቱ አይጸናም።

13 የሰሜን ንጉሥ ከመጀመሪያው የሚበልጥ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባል፤ ከብዙ ዓመትም በኋላ በትጥቅ እጅግ ከተደራጀ ታላቅ ሰራዊት ጋር ተመልሶ ይመጣል።