ዳንኤል 2:28-34 NASV

28 ነገር ግን ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጦአል፤ በዐልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ በአእምሮህ የነበረው ሕልምና ራእይ ይህ ነው፦

29 “ንጉሥ ሆይ፤ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ ወደ ፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር፤ ምስጢርን ገላጭ የሆነውም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አሳየህ።

30 ይህ ምስጢር ለእኔ የተገለጠው፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትርጒሙን እንድታውቅና በአእምሮህ ታሰላስለው የነበረው ነገር ምን እንደሆነ ትረዳ ዘንድ ነው።

31 “ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ፤

32 የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤

33 ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ።

34 ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም።