32 የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤
33 ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ።
34 ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም።
35 ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ።
36 “ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጒሙን ለንጉሥ እንናገራለን።
37 ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤
38 የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ።