ዳንኤል 3:15-21 NASV

15 አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእምቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”

16 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጒዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም።

17 ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።

18 ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”

19 ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድ አዘዘ፤

20 ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ።

21 እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ።