ዳንኤል 3:6-12 NASV

6 ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”

7 ስለዚህ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው ሰገዱ።

8 በዚህ ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቈጣሪዎች ወደ ፊት ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፤

9 ንጉሥ ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!

10 ንጉሥ ሆይ፤ አንተ እንዲህ ብለህ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ድምፅ የሰማ ሁሉ ለወርቁ ምስል ተደፍቶ መስገድ አለበት፤

11 ማንም ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ባይሰግድ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

12 ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያገለግሉም፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።”