ዳንኤል 4:16-22 NASV

16 አእምሮው ከሰው አእምሮ ይለወጥ፤ የእንስሳም አእምሮ ይሰጠው፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት።

17 “ ‘ውሳኔው በመልእክተኞች ተገልጾአል፤ ፍርዱም በቅዱሳኑ ተነግሮአል፤ ይኸውም፣ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።’

18 “እኔ ናቡከደነፆር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፤ በመንግሥቴ ካሉ ጠቢባን ሁሉ አንዳቸውም ሊተረጒሙልኝ ስላልቻሉ፣ ምን ማለት እንደሆነ ንገረኝ። አንተ የአማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ልትተረጒምልኝ ትችላለህ።

19 ከዚያም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል ለጥቂት ጊዜ በጣም ታወከ፤ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም፣ “ብልጣሶር ሆይ፤ ሕልሙም ሆነ ትርጒሙ አያስደንግጥህ” አለው።ብልጣሶርም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ሕልሙ ለሚጠሉህ ይሁን፤ ትርጒሙም ለጠላቶችህ!

20 እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣

21 ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጎጆ መሥሪያ ያለው፣

22 ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ፤ ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ።