ዳንኤል 7:18-24 NASV

18 ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም ይይዙታል።

19 “ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጒም ማወቅ ፈለግሁ።

20 ደግሞም በራሱ ላይ ስላሉት ዐሥር ቀንዶች፣ ከመካከላቸው ብቅ ስላለው ቀንድና ከዚሁ ቀንድ ፊት ስለ ተነቃቀሉት ሦስት ቀንዶች፣ እንደዚሁም ከሌሎች ስለ በለጠው የሰው ዐይኖች የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ስለ ነበሩት ስለ ዚሁ ቀንድ ማወቅ ፈለግሁ።

21 እነሆም፤ ይህ ቀንድ በቅዱሳን ላይ ጦርነት ዐውጆ አሸነፋቸው፤

22 ይህም የሆነው ጥንታዌ ጥንቱ እስኪመጣና ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪፈርድላቸው ድረስ ነበር፤ ከዚያም የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን የሚወርሱበት ዘመን መጣ።

23 “እርሱም እንዲህ አለኝ፣ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛው መንግሥት ነው። ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላውንም ምድር እየረገጠና እያደቀቀ ይበላል።

24 ዐሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚወጡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ከእነርሱ የተለየ ሌላ ንጉሥ ይነሣል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያንበረክካል።