ዳንኤል 9:17-23 NASV

17 “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ።

18 አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው።

19 ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።”

20 እኔም እየተናገርሁና እየጸለይሁ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኀጢአት እየተናዘዝሁ፣ ስለ ቅዱስ ተራራውም እግዚአብሔር አምላኬን እየለመንሁ፤

21 እየጸለይሁም ሳለሁ፣ በመጀመሪያው ራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ በፍጥነት እየበረረ ወደ እኔ መጣ።

22 እርሱም እንዲህ ብሎ አስረዳኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ መጥቻለሁ።

23 አንተ እጅግ የተወደድህ ስለ ሆንህ፣ ገና መጸለይ ስትጀምር መልስ ተሰጥቶአል፤ እኔም ይህን ልነግርህ መጣሁ። ስለዚህ መልእክቱን ልብ በል፤ ራእዩንም አስተውል።