ዳንኤል 9:19-25 NASV

19 ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።”

20 እኔም እየተናገርሁና እየጸለይሁ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኀጢአት እየተናዘዝሁ፣ ስለ ቅዱስ ተራራውም እግዚአብሔር አምላኬን እየለመንሁ፤

21 እየጸለይሁም ሳለሁ፣ በመጀመሪያው ራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ በፍጥነት እየበረረ ወደ እኔ መጣ።

22 እርሱም እንዲህ ብሎ አስረዳኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ መጥቻለሁ።

23 አንተ እጅግ የተወደድህ ስለ ሆንህ፣ ገና መጸለይ ስትጀምር መልስ ተሰጥቶአል፤ እኔም ይህን ልነግርህ መጣሁ። ስለዚህ መልእክቱን ልብ በል፤ ራእዩንም አስተውል።

24 “ዐመፃን ለማስቆም፣ ኀጢአትን ለማስወገድ፣ በደልን ለማስተሰረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራእይንና ትንቢትን ለማተምና፣ እጅግ ቅዱስ የሆነውን ለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔ ታውጇል።

25 “ይህንን ዕወቅ፤ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል። ኢየሩሳሌም ከጐዳናዎቿና ከቅጥሮቿ ጋር ትታደሳለች፤ ይህ የሚሆነው ግን በመከራ ጊዜ ነው።