17 አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም።
18 ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
19 ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፣ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፣ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።
20 ወንድሞች ሆይ፤ በአስተሳሰባችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ፤ በአስተሳሰባችሁ ግን ጐልማሶች ሁኑ።
21 በሕግም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፣በባዕዳንም አንደበት፣ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፤”ይላል ጌታ።
22 ስለዚህ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም።
23 እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፣ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፣ አብደዋል አይሉምን?