1 አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክ ሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤
2 የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው።
3 እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤
4 ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤
5 ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤
6 ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል።