16 ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ።
17 በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል።
18 ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው።
19 እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ።
20 አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ።
21 እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ።
22 ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ።