1 ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ የመጣነው ለከንቱ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
2 እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደር ስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን።
3 የምናቀርበው ልመና ከስሕተት ወይም ከክፉ ዐላማ ወይም እናንተን ለማታለል ከመፈለግ የመነጨ አይደለም።
4 ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ብለን አይደለም።