1 በአዳኛችን በእግዚአብሔር፣ ተስፋችንም በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤
2 በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፤ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት፣ ሰላምም ይሁን።
3 ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ ዐደራ እንዳልሁህ፣ አንዳንድ ሰዎች ከእንግዲህ የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታዛቸው ዘንድ በዚያው በኤፌሶን ተቀመጥ፤
4 ደግሞም ለተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልዶች ታሪክ ራሳቸውን አሳልፈው እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እነዚህ ነገሮች በእምነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሥራ ይልቅ ክርክርን ያነሣሣሉ።
5 የዚህ ትእዛዝ ዐላማ ግን ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው።
6 አንዳንዶች ከእነዚህ ነገሮች ዘወር ብለው ወደ ከንቱ ንግግር ተመልሰዋል።