1 ጢሞቴዎስ 1:7-13 NASV

7 የሕግ መምህራን ለመሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ስለሚናገሩት ወይም አስረግጠው ስለሚሟገቱለት ነገር አያውቁም።

8 ነገር ግን ሰው በአግባቡ ከተጠቀመበት፣ ሕግ መልካም መሆኑን እናውቃለን።

9 ደግሞም ሕግ የተሰጠው ለጻድቃን ሳይሆን፣ ለሕግ ተላላፊዎችና ለዐመፀኞች፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ለሌላቸውና ለኀጢአተኞች፣ ቅድስና ለሌላቸውና እግዚአብሔርን ለሚንቁ፣ አባትና እናታቸውን ለሚገድሉ፣ ለነፍሰ ገዳዮች መሆኑን እናውቃለን፤

10 እንዲሁም ለዘማውያን፣ ከወንድ ጋር ለሚተኙ ወንዶች፣ ሰውን ለሚሸጡና ለሚገዙ፣ ለውሸተኞች፣ በሐሰት ለሚምሉ፣ ጤናማ የሆነውን ትምህርት ለሚጻረሩ ሁሉ ነው፤

11 ይህ ጤናማ ትምህርት ቡሩክ እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው።

12 በአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ የቈጠረኝን፣ ብርታት የሰጠኝን ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ።

13 ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ የነበርሁ ብሆንም፣ ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረት ተደርጎልኛል፤