2 የሚያምኑ ጌቶች ያሏቸውም፣ ወንድሞች ስለሆኑ የሚገባቸውን ክብር አይንፈጓቸው፤ ይልቁንም በአገልግሎታቸው የሚጠቀሙ አማኞችና ወዳጆቻቸው ስለሆኑ የበለጠ ሊያገለግሏቸው ይገባል። እነዚህን ነገሮች አስተምር፤ ምከርም።
3 ማንም የሐሰት ትምህርት ቢያስተምር፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጤናማ ቃልና እውነተኛ መንፈሳዊነትን ከሚያጐለብት ትምህርት ጋር የማይስማማ ቢሆን፣
4 ያ ሰው በትዕቢት ተወጥሮአል፤ አንዳችም አያስተውልም። ስለ ቃላት ለመከራከርና ለመጣላት ክፉ ጒጒት አለው፤ እነዚህም ቅናትን፣ ጥልን፣ ስድብን፣ መጥፎ ጥርጣሬን ያስከትላሉ፤
5 እውነትን በተቀሙና መንፈሳዊው ነገር ትርፍ ማግኛ በሚመስላቸውና አእምሮ በጐደላቸው ሰዎች መካከል የማያባራ ንትርክ ያመጣሉ።
6 ነገር ግን እውነተኛ መንፈሳዊነት ባለን ነገር ከመርካት ጋር ትልቅ ትርፍ ነው።
7 ምክንያቱም ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም።
8 ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል።