9 የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
10 ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤
11 በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር።
12 አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ባበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።
13 ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ።
14 ታዛዦች ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ።
15 ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤