2 ቆሮንቶስ 12:11-17 NASV

11 በመመካቴ ሞኝ ሆኛለሁ፤ ለዚህም ያበቃችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ ስለ እኔ መመስከር የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ። ደግሞም እኔ ከምንም የማልቈጠር ብሆንም፣ “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም አላንስም።

12 የእውነተኛ ሐዋርያ ምልክቶች በመካከላችሁ ተደርገዋል፤ እነርሱም በትዕግሥት መጽናት፣ ምልክቶች፣ ድንቅ ነገሮችና ታምራት ናቸው።

13 በእናንተ ላይ ሸክም ካለመሆኔ በቀር፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በምን አነሳችሁ? ይህን በደሌን ይቅር በሉኝ።

14 ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ስመጣ በምንም ነገር ሸክም አልሆንባችሁም፤ እኔ እናንተን እንጂ ከእናንተ ምንም አልፈልግምና፤ ደግሞም ወላጆች ለልጆች ገንዘብ ያከማቻሉ እንጂ ልጆች ለወላጆች አያከማቹም።

15 እኔ ግን ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ብሰጥ ደስ ይለኛል፤ ታዲያ እኔ የምወዳችሁ ይህን ያህል ከሆነ፣ እናንተ የምትወዱኝ በጥቂቱ ነውን?

16 የሆነው ሆኖ ሸክም አልሆንሁባችሁም፤ ነገር ግን በተንኰልና በዘዴ ያጠመድኋችሁ ሳይመስላችሁ አልቀረ

17 ለመሆኑ ወደ እናንተ በላክኋቸው ሰዎች አማካይነት በአንዱ እንኳ በዘበዝኋችሁን?