2 ቆሮንቶስ 12:6-12 NASV

6 መመካት ብፈልግ እንኳ እንደ ሞኝ መቈጠር የለብኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው። ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው በላይ እንዳይገምተኝ ከመመካት እቈጠባለሁ።

7 ከዚህ ታላቅ መገለጥ የተነሣ እንዳልታ በይ የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ።

8 ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት፤

9 እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።

10 ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።

11 በመመካቴ ሞኝ ሆኛለሁ፤ ለዚህም ያበቃችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ ስለ እኔ መመስከር የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ። ደግሞም እኔ ከምንም የማልቈጠር ብሆንም፣ “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም አላንስም።

12 የእውነተኛ ሐዋርያ ምልክቶች በመካከላችሁ ተደርገዋል፤ እነርሱም በትዕግሥት መጽናት፣ ምልክቶች፣ ድንቅ ነገሮችና ታምራት ናቸው።