1 ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን።
2 የደረሰባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም ደስታቸው ግን የላቀ ነበር፤ ድኽነታቸው ብርቱ ቢሆንም ልግስናቸው ግን የበዛ ነበር።
3 እንደ ዐቅማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከዐቅማቸው በላይ በፈቃዳቸው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁ።
4 እነርሱም ቅዱሳንን ለመርዳት በሚደረገው አገልግሎት ለመሳተፍ ዕድል ያገኙ ዘንድ አጥብቀው ይለምኑን ነበር።
5 እኛ ከጠበቅ ነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ።
6 ስለዚህ ቲቶ፣ በእናንተ መካከል ቀደም ሲል የጀመረውን የልግስና ሥራ ከፍጻሜ እንዲያደርስ ለምነነው ነበር።
7 እናንተም በሁሉ ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በዕውቀት፣ በፍጹም ትጋትና ለእኛም ባላችሁ ፍቅር ልቃችሁ እንደ ተገኛችሁ፣ በዚህም የቸርነት ሥራ ልቃችሁ እንድትገኙ ዐደራ እንላችኋለን።