5 ስለዚህ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡና ከዚህ በፊት ለመስጠት ቃል የገባችሁትን ስጦታ አጠናቃችሁ እንድትጠብቋቸው፣ እነርሱን መለመን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ በልግስና ለመስጠት ያሰባችሁት ነገር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተዘጋጀ ይሆናል።
6 ይህን አስታውሱ፤ ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል።
7 እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል።
8 ሁል ጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤
9 ይህም፣“በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል”ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
10 ለዘሪ ዘርን፣ ለመብላት እንጀራን የሚሰጥ እርሱ የምትዘሩትን አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል።
11 ሁል ጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል።