2 ዮሐንስ 1 NASV

1 ሽማግሌው፤በእውነት ለምወዳት እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወዷት ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፤

2 በውስጣችን ከሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ከሚሆን እውነት የተነሣ፣

3 ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።

4 ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአብ በተሰጠን ትእዛዝ መሠረት በእውነት ጸንተው እየሄዱ በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል።

5 አሁንም እመቤት ሆይ፤ ከመጀመሪያ የነበረችውን እንጂ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍልሽም፤ ይኸውም እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ ነው።

6 ይህም ፍቅር፤ በትእዛዛቱ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው። ትእዛዙም ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት በፍቅር እንድትኖሩ ነው።

7 ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

8 እናንተም የደከማች ሁበትን ዋጋ እንዳታጡ፣ ነገር ግን ሙሉ ሽልማት እንድትቀበሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

9 በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው።

10 ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ይህንንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤

11 የሚቀበለው ሰው፣ የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና።

12 የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በወረቀትና በቀለም እንዲሆን አልፈልግም፤ ዳሩ ግን ደስታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት ላነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

13 የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።

ምዕራፎች

1