1 የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ስምዖን ጴጥሮስ፤በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤
2 እግዚአብሔርንና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
3 በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል።
4 ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ካለው ምግባረ ብልሹ ሕይወት አምልጣችሁ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ በእነዚህ ነገሮች አማካይነት እጅግ ታላቅና ክቡር የሆነውን ተስፋ ሰጥቶናል።